Bible Interpretation, Amharic Student Workbook
/ 5 9
የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ-አፈታት
ይህም የእኛ የጥሞና ክፍል መነቃቃትን፣ ተሃድሶ እና እረፍትን ለማምጣት እግዚአብሔር የሚጠቀመውን የሰውን ውስጣዊ ህይወት አይነት እና ተነሳሽነት ይመዘግባል። “ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።” በዚህ ክፍል መሠረት ዕዝራ ጌታን ወክሎ ሦስት ነገሮችን ለማድረግ እራሱን “ነፍሱን” አዘጋጅቶ ነበር። በመጀመሪያ፣ ዕዝራ የጌታን ሕግ ለማጥናት ልቡን አቅንቷል። በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተከፈለ ልብ፣ የሚያንቀላፋ አይን አይኖርም፣ ነገር ግን በስነስርዓት የሆነ፣ ከጥልቅ ስሜት የመነጨ፣ የእግዚአብሔር ሕግ ላይ ያተኮረ ጥናት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ በሌላ መንገድ ለመማር አይቻልም፣ ውድ ማዕድናት ፈላጊዎች ወርቅ እንደሚፈልጉ የጌታን እውቀት ሳይፈልጉ፣ የተደበቀው ምስጢር እና የጽሑፉ ትርጉም በቀላሉ ሊገኝ ወይም ሊገነዘብ አይችልም (ምሳ. 2.1-9)። ሰነፍ፣ ስነ-ስርዓት የሌለው ልብ በክርስቶስ ያለውን የማዳን እቅድ በተመለከተ የእግዚአብሔርን ጥበብ ባለጠግነት ፈጽሞ ሊያውቅ አይችልም። ሁለተኛ፣ ይህን ለማድረግ ልቡን ወስኗል። በቀላል አነጋገር ዕዝራ የሚኖረው ለማጥናት አልነበረም፤ ይልቁንም ለመኖር ያጠና ነበር። የእግዚአብሔር ቃል አላማ እምነትን፣ መታዘዝን፣ ፍቅርን እና አገልግሎትን በሚመለከት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መስማት ብቻ አይደለም። ዓላማው ቃሉን ማድረግ ነው፣ የጽሑፉም በረከት ለሚያሰላስሉት ብቻ ሳይሆን በትህትና እና በትጋት ለእግዚአብሔር ቃል ምላሽ ለሚሰጡት ነው (ያዕቆብ 1.22-25)። የእግዚአብሔር ጥበብ በቅዱስ ቃሉ ውስጥ ፈቃዱን ለሚፈጽሙ ሰዎች ይመጣል (መዝሙረ ዳዊት 111፡10 - “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ ለሚያደርጓትም ሁሉ ደኅና ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።”)። በመጨረሻም ዕዝራ “ህጉንና ሥርዓቱን በእስራኤል ለማስተማር” ልቡን አቅንቷል። የእግዚአብሔር ቃል በጥናት የተካነ እና በመታዘዝ ከተፈጸመ በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ አገልግሎቱን በማስተማር አገልግሎት ለመወጣት ዝግጁ ነው። ዕዝራ የቃሉን አቀራረብና አገልግሎቱን በሚመለከት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች በተገቢው ቅደም ተከተል ነበር፡- ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕግ ለማጥናት፣ ለመፈጸምና ከዚያም ለማስተማር ራሱን አዘጋጅቷል። እንዲህ ዓይነቱ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ እና የልብ ዝግጅት ቅዱሳን፣ ክርስቲያን ሰራተኞች፣ ነቢያት እና ሐዋርያት የተጠሩበት እውነተኛ ነገር ነው። ትኩረቱ በተልዕኮው፣ ወይም በሥራው፣ ወይም በበረከቱ፣ ወይም በስጦታዎቹ ላይ አይደለም። ትኩረቱ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ነው - እሱን በማጥናት፣ በመማር፣ በተግባር ላይ በማዋል፣ እንዲሁም አንዴ ያወቁትን እና የታዘዙትን ቃል በፍላጎት እና በግልጽነት ማጋራት። በእዝራ አገልግሎት ውስጥ የሆነውም በትክክል ይኸው ነው: በልቡ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ምክንያት፣ ለእግዚአብሔር ህዝብ መነቃቃትን እና መታደስን ለማምጣት እግዚአብሔር በብርቱ ተጠቅሞበታል፤ በመጨረሻም ህዝቡን ለመሲሁ መምጣት ለማዘጋጀት ለሚደረገው እንቅስቃሴ መሰረት ጥሏል። ይህ ሁሉ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ፍቅር ያለው አንድ ግለሰብ ልቡን ለቃሉ ስላዘጋጀ ነው። ለእግዚአብሔር ክብር ቃሉን ለማጥናት፣ ለመፈጸም እና ለህዝቡ ለማስተማር ልብህ በእግዚአብሔር ፊት ተነሳስቷል? በራስህ ላይ ታተኩራለህ - በስጦታዎችህ፣ በበረከትህ፣ በእድሎችህ፣ ወይስ የእግዚአብሔርን ቃል በህይወትህ ውስጥ በተግባር ለማዋል እና በመንፈስ ቅዱስም ነጻነት ቃሉን ለእግዚአብሔር ህዝብ ለማስተማር ግልጽ ፍላጎት አለህ? የእግዚአብሔርን ቃል በትሕትናና በድፍረት ከሰበከ ከዚህ ሰው ምሳሌ እንውሰድ፤ አገልግሎቱ የተጀመረው በታላቅ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ቃል የተማረውን የእርሱን ፈቃድ ለማወቅና ለመፈጸም ከልቡ በመነሳቱ ነው። ‘በጌታ ስም ለሚያከናውኑት ፍሬያማ አገልግሎት’ ሁሉ ምሳሌ የሚሆን ነው።
2
Made with FlippingBook - Online Brochure Maker